አራተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር

ህወሓት/ኢህአዲግ ሥልጣን ከያዘ አራተኛውን ጠ/ሚ/ር በትናንትናው ዕለት እንደመረጠ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሰበር ዜና ብሎ በጥንቃቄ የተዘጋጀውን መልዕክት ባልተለመደ ሁኔታ ሶስት ጊዜ ደጋግሞ አንብቦልናል። በደንብ እንዲገባን ታስቦ ሳይሆን አይቀርም። እርግጥ ፓርቲው ሊቀ መንበሩን ቢሆንም የመረጠው የፓርላማ ሥርዓትን በሚከተሉ ሀገሮች እንደሚደረገው የገዢው ፓርቲ ሊቀ መንበር የሀገሪቱ መሪ ይሆናል። ሥርዓቱ የተሟላ እንዲሆን በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰብስቦ ይሁንታውን ይሰጣል ብለን እንጠብቃለን።

በከፍተኛ ምስጢር ሲካሄድ የከረመው ስብስባ ስላለቀ ሰሞኑን አንዳንድ ነገር መስማታችን አይቀርም። መቼም መቶ ምናምን ሰው የተሳተፈበት ስብሰባ ምስጢር ሊሆን አይችልም።

“የአክሱም ታሪክ ለወላይታ ምኑ ነው” 

በጠ/ሚ/ር መመራት የጀመርንበት ሁኔታ የራሱ የሆነ ታሪክ አለው። ህወሓት/ኢህአዲግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ  ጠ/ሚ/ር የነበረው አቶ ታምራት ላይኔ ሲሆን ራሱን የፕሬዚዳንትነት ካባ ያጎናፀፈው ደግሞ መለስ ዜናዊ ነበር።  “የአክሱም ታሪክ ለወላይታ ምኑ ነው” እያለ ሲፎልል የነበረው ህወሓት ራሱ ለሀገሪቱ ባስተዋወቀው የዘር ፖለቲካ ምክንያት በምዕተ ዓመትም ቢሆን የማሸነፍ እድሉ ዜሮ ከመቶ እንደሆነ ወዲያው ተረድቶታል።

ስለዚህ በመላ ሀገሪቱ እየዞሩ የማያውቁትን ሕዝብ ምረጡኝ ከማለት የፓርላማ ሥርዓት የሚባል ጂኒ ቁልቋል አስተዋውቆ “እኖርበት ነበር” ባለው መንደር ራሱን ያለተቀናቀኝ አስመርጦ ራሱ ባቋቋመው ፓርላማ አባል መሆን ብቻ በቂው ነበር። ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ ፀደቀ ከተባለበት ከ1987 ጀምሮ ፕሬዚዳንቱ ራሱን ወደ ጠ/ሚ/ርነት ቀይሮ ሀገሪቱንም የይስሙላ ፓርላማ ሥርዓት ተከታይ አደረጋት።

ብልሃቱ ለመለስ ሰርቷል። ያለምንም ተቀናቃኝ ከሃያ አመት በላይ በሃገሪቱ  ነግሷል። ሲያልፍም ራዕይ የሌለው የሱን “ሌጋሲ” የሚያስቀጥል መሪ ትቶልን ሄዷል።

“ጠንካራ ተቃዋሚ” 

አሁን ግን ጊዜው የተቀየረ ይመስላል። ኦነግን የመሳሰሉ የኦሮሞ ድርጅቶችን ለመምታትና በክልሉ የህወሓት አፍ እንዲሆን የተፈጠረው ኦህዲድ ከማንም “ጠንካራ ተቃዋሚ” ገዝፎ ይባስ ብሎ ደግሞ አጀንዳውን አስፍቶ ከች ብሏል። ኢትዮጵያውያን ለምርጫ ባይታደሉም ምናልባት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብ በአርምሞ የተስማማበት መሪ ብቅ ያለ ይመስላል። በአንፃሩም ህወሓት ያልተስማማውን ለመንቀፍ የሚሄድበትን ርቀት በዶ/ር አብይ ላይ በከፈተው የማጥላላት ዘመቻ ኣሳይቷል ። የሀገሪቱ መረጃና ደህንነት ክፍል ዕውነተኛ ሥራ ምን እንደነበር በግልፅ የታየበት ጊዜ ነበር።ዶ/ር አብይ ቂም መያዝ አይችልም። ይህንን ማስተካከል ግን ይጠበቅበታል። ከእንግዲህ መሪነቱ ለኦህዲድ ብቻ አይደለም። መሪነቱ ለሚቃወሙትም እንዲሁም ጧት ማታ ሰብዕናውን ሲገድሉ ለነበሩትም ነው።ለውጥ ፈላጊ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ተዓምር እንዲሰራ ይጠብቀዋል። እንደውም “ምነው በቀረብኝ” የሚልበት ጊዜ ሩቅ ሁሉ ላይሆን ይችላል።

የዘር ፖለቲካ ትሩፋት

• አዲሱ ጠ/ሚ/ር ካቢኔውን ሲያዋቅር በርካታ ጊዜ የሚያጠፋው የብሄሮችን ስብጥር ሲያመጣጥን ይሆናል።

• በዚህ ሁሉ ዓመፅና የፖለቲካ ሽኩቻ እስከመኖራቸውም የረሳናቸው ፕሬዚደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የብሔር ተዋፅኦ ሰለባ ይሆናሉ። በድጋሚ አይመረጡም።

ሰዎች ባለ ሥልጣን ሲሆኑ ወይም ከፍተኛ ሃላፊነት ሲሰጣቸው “ሹመት ያዳብር” ይባል ነበር። የሚዳብረው ለጊዜው ይቆየንና የሀገሪቱ አዲስ ፊት የሆነውን ዶ/ር አብይ አሕመድ መልካም ዕድል እንመኝለት።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: