በኤችአር 128 ጉዳይ ማንን እንቀበል?

በቅርቡ የአሜሪካ ኮንግሬስ ኤችአር 128 የተባለ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አስመልክቶ ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህ ጉዳይ ላይ በመንግሥትና ውሳኔው እንዲተላለፍ ይጎተጉቱ በነበሩ የሰብዓዊ መብት አራማጆች እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው። ውሳኔውን የመብት ተሟጋቾችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እንደ ድል ሲቆጥሩት ከገዢው ፓርቲ ጎን የተሰለፉት ሲያጣጥሉት ተስተውለዋል።

ውሳኔው

የውሳኔው ወረቀት በነጋሪት ጋዜጣ ቅኝት የተፃፈ ሲሆን የሕግ አንቀፆችን መረዳት ጋራ ለሚሆንብን የተለየ ነገር ማውጣት ቀላል አይደለም። የሕግ ባለሙያዎች ማብራሪያ ጉዳዩን ይበልጥ ለመረዳት እጅጉን አስፈላጊ ነው። ይሁንና በግልፅ ከሚታዩት ጥቂት አንቀፆች መካከል፥መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ፥ በ2001 ዓም የወጡት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጆች እንዲሻሻሉ ወይም እንዲሰረዙ፥ ተቃዋሚዎች የሰብዓዊ መብት አራማጆችና ጋዜጠኞች  እንዲፈቱ፥ የፀጥታ ሃይሎች ያልተመጣጠነ እርምጃ እንዲቆም ግድያና ድብደባ የፈፀሙ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲሁም የሀገሪቱን የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሁኔታ አስመልክቶ በተባበሩት መንግሥታት በሚሰየም ገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባል።

ረጅም ብትር ባይመቱበት ያስፈራሩበት 

የውሳኔ ሃሳቡን የሚደግፉ ወገኖች አሜሪካ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያላትን ተቆርቋሪነት በግልፅ ያሳየ ነው ይላሉ። እስከዛሬ አሜሪካንን ስንጎተጉት ሰሚ አግኝተን አናውቅም ነበር። በመጨረሻ ሮሮእችንን አዳመጡን ያሉም አሉ። በተጨማሪም መንግስት የመብት ጥሰት ፈፃሚ ስለመሆኑ እውቅና የተሰጠበት ሰነድ አድርገውም ያዩታል። አንድ አስተያየት ሰጪ “ረጅም ብትር ባይመቱበት ያስፈራሩበት” ሲሉ የውሳኔውን አጠቃላይ እንድምታ አስቀምጠውታል። ውሳኔው ሲፀድቅ ለመስማትም የአሜሪካ ምክር ቤት ድረስ ሄደው ደስታቸውን የገለፁ ዜጎችም ነበሩ።

የመንግሥት ሰዎች

“ይሄ ሃሳብ ብቻ ነው ሕግ ሆኖ ለመውጣት ገና ይቀረዋል። ስለዚህ አስገዳጅነትም የለውም” እያሉ ከማጣጣል አንስቶ “በፀረ ሽብር ዘመቻ ላይ ከአሜሪካ ጋር ያለኝን ትብብር አቋርጣለሁ” የሚል ዛቻ እስከመሰንዘር በተለያዩ ቀላጤዎች እየተነገረ ነው። በይፋ የመንግሥት አፍ በመሆን እያገለገሉ ያሉት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ “ወቅታዊ ያልሆነና ያልተገባ” ብለው “ይሄኛው ውሳኔ የአሜሪካ መንግሥት አቋም ነው ብለን መደምደም አንችልም” ሲሉ አክለዋል። ከ200 አመት በላይ የመምረጥና የመመረጥ ባህል በዳበረበት ሀገር ውስጥ ያሉ የሕዝብ ተወካዮች ያሳለፉት ውሳኔ እንዴት የመንግሥት አቋም እንደማይሆን ግራ የሚያጋባ ነው። ሚኒስትሩ ሲቀጥሉ “የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚወተውቷቸው ተቃዋሚ የዳያስፖራ አባላትም ስላሉ እነሱን ለማስደሰት የተወሰደ ነው” ይላሉ። ከ325 ሚሊየን ሕዝብ በላይ በሚኖርባት አሜሪካ የኢትዮጵያ “ተቃዋሚ የዳያስፖራ አባላት” ምን ያህል ቁጥርና ተፅዕኖ ቢኖራቸው እንደሆነና እነሱንም ለማስደሰት የኮንግሬስ አባላት የሚሰበሰቡበትን ሁኔታ የሚያውቁት ዶክተሩ ብቻ ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ መለስ አለም “የኮንግሬሱ ውሳኔ የስቴት ዲፓርትመንት ውሳኔ አይደለም፥ የሴኔት አይደለም፥ የፔንታጎን አይደለም። የኮንግሬስ አባላቱ ውሳኔ ነው።” ሲያጠቃልሉት ደግሞ ውሳኔው “የሚያመጣው ምንም ተፅዕኖ የለም” ብለዋል። ባወጡት መግለጫ ግን ውሳኔውን በፅኑ ተቃውመው “ሉዓላዊነታችንን ይዳፈራል” ብለው ደምድመዋል። ምንም ተፅዕኖ የሌለው ውሳኔ እንዴት ሉዓላዊነትን እንደሚዳፈር ግልፅ አይደለም። በነገራችን ላይ ሰብዓዊ መብትን አስመልክቶ አቶ መለስ አለም ከቢሯቸው 12ሺህ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ስላለ ጉዳይ አስተያየት ከመስጠታችው በፊት በግል በግርፊያ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደነበር ሰሞኑን በፍርድ ቤት የተገለፀውን ጉዳይ መስመር ቢያስይዙት ለመስሪያ ቤታቸውም ገፅታ በጠቀመ ነበር።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ካሳ ተክለብርሃን ሥራቸውን ያሟሹት ኮንግሬሱ ውሳኔውን እንዳያሳልፍ አጥብቀው በመማጠን ነበር። አሁን በሀገሪቱ በመካሄድ ላይ ያለውን የለውጥ ጅምር ያደናቅፋል ሲሉ ውሳኔው ውድቅ ኢንዲሆን የላኩት ደብደቤ ሰሚ አላገኘም።

በሕወሓት ድረገፅ የቀረበ ሃተታ ደግሞ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ አምርሮ በመቃወም በልማቱ ዘርፍ ምንም ድርሻ እንዳልነበራት በመግለፅ በዚህ ረገድ ቻይናን ያወድሳል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል፥ህዩመን ራይትስ ወች፥ፍሪደም ሃውስ፥ቢቢሲ፥የአሜሪካ ድምፅ አማርኛ አገልግሎት፥ሲኤንኤን፥ኢሳትና ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክን በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ የከፈቱ ብሎ ያወግዛቸዋል። ውሳኔውም የተላለፈው በሀገሪቱ ጉዳይ ፈፅሞ የማያገባቸው ዜግነታቸውን ለጥቅም ብለው በቀየሩ ሀገሪቱንም ለተሻለ ተጫራች ለመሸጥ የቋመጡ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ገለመሌ እያለ ይቀጥልና ለውሳኔው መፅደቅ የኔዎ ሊበራል አስተሳሰብ የተጠናወታቸውን ግለሰቦችና ተቋማትን ተጠያቂ ያደርጋል።

አሁን ጥያቄው ኤችአር 128 ምንም ተፅእኖ የማያመጣ ከሆነ ይህ ሁሉ የመግለጫ ጋጋታ ለምን ያስፈልጋል ነው።

ወትዋቾቹ የት ጠፉ?

መቀመጫው ዋሺንግተን ዲሲ የሆነው ዲኤልኤ ፓይፐር በወር 50ሺ ዶላር እየተከፈለው ለኢትዮጵያ መንግሥት ሲሰራ እንደነበር ይታወቃል። ድርጅቱ ምርጫ 97ን ተከትሎ  በአሜሪካ ኮንግሬስ ተረቅቆ የነበረውን ኤችአር 2003 የተባለ ተመሳሳይ የውሳኔ ሃሳብ እንዲወድቅ በማድረጉ ረገድ ጉልህ ድርሻ ነበረው። ይሁንና ድርጅቱን የቀጠሩት በወቅቱ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ሲዛወሩ በነበረው ግምገማ አግባቢው ያስገኘው ውጤት አጥጋቢ አይደለም በሚል ሌላ ድርጅት እንዲፈለግ መወሰኑ ለመንግስት ቅርበት ያለው ጋዜጣ በአንድ ወቅት የዘገበው ጉዳይ ነው።

ከዛ ወዲህ ለሰባት አመታት ያህል በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ እዛው ዋሺንግተን ዲሲ ከሚገኝ ኤስጂአር ኤልኤልሲ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር በወር 150ሺ ዶላር ክፍያ የውትወታ ሥራው እንዲቀጥል ተፈራርመው ነበር። ድርጅቱ ምጥ ይግባ ስምጥ የሚታወቅ ነገር የለም። ሰሞኑንም ድምፁን አልሰማንም። ወይ ከዚህ የተለየ ተልዕኮ ተሰጥቶት እንደሆነም አይታወቅም።

ቀጣዩ ሁኔታስ

አዲሱ ጠ/ሚ/ር እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲሰጡ አልተደመጠም። በውሳኔ ሃሳቡ ላይ የተነሱትን የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ችግሮችን ባገኙት አጋጣሚ በቀጥታም በተዘዋዋሪም አንስተዋል። ከዛም ባለፈ ከጥቂት ወራት በፊት በአሸባሪነት ተወንጅለው እስር ቤት ተወርውረው ከነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ጋር ራት ታድመዋል። የኮንግሬስ አባላቱም እርምጃዎቻቸውን በአዎንታ እያዩ እንደሆነ አመልክተዋል። ኤችአር 128 የውሳኔ ሀሳብ የሰብዓዊ መብት ይዞታን ይበልጥ እንዲያሻሽሉ በማሳሰቢያነት ይዩት ወይም እንደቀድሞዎቹ ማንም አያገባውም ብለው ይቀጥሉ የሚታይ ጉዳይ ይሆናል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: