የኢኤንኤን አስከሬን ምርመራ

ኢትዮጵያን ኒውስ ኔትወርክ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ የለውጡ የመጀመሪያ ሰለባ ሆኗል። አብሮም ከመቶ የሚበልጡ ሰራተኞች ተበትነዋል። ኢኤንኤን በ2008 ይከፈት እንጂ ባለቤቱ አቶ ቢኒያም ከበደ ላለፉት ሀያ ዓመታት ኢትዮጵያ ፈርስት የተባለ ወገንተኝነት የሚታይበት ድረገፅ ባለቤት ናቸው። ድረገፁ ከመንግሥት ስለሚያገኘው ድጎማ ለጊዜው በግልፅ የተነገረ ባይኖርም ድጋፍ ይደረግለት እንደነበረ የሚያመለክቱ ፍንጮች ግን አሉ።

ለሌሎች የተዘጉ በሮች ለአቶ ቢኒያም ክፍት ነበሩ። በዚህ የተነሳ በርካታ ፕሮግራምችን ሠርተዋል። እንደ ሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊን የመሣሠሉ ግለሰቦችን ዒላማ ያደረጉ ጥልቅ የምርመራ ዘገባዎችን አቅርበዋል። እርግጥ ነው በሥራዎቹ ላይ የበላይ አካላት ድጋፍ አሻራ ይታያል። የቀድሞውን ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊን በጽሕፈት ቤታቸው ቃለመጠይቅ ካደረጉ ጥቂት ሰዎች አንዱ ናቸው። ይሄንን እድል የመንግሥት ጋዜጠኞችም አያገኙትም። እነዚህን ሥራዎች ለመከወን ከካናዳ እየተመላለሱ የመጓጓዣ፥ የማረፊያ፥ ደረጃቸውን የጠበቁ የቴሌቪዥን ካሜራዎች ከነአባሪያቸው መግዣ ፤ እንዲሁም የሠራተኞች ክፍያን ከኪሳቸው እያወጡ ይከፍሉ ነበር ለማለት ያስቸግራል። የድረ ገፃቸውም ተከታይ ብዛት የማስታወቂያ ገቢ ከዝርዝር ፍራንክነት የሚያልፍ አይደለም። አሌክሳ በተባለው የተነባቢነት ደረጃ አውጪ እንኳ ስለ ኢትዮጵያ ፈርስት የተቀመጠው ቁጥር ለመጠቀስም አይመችም። ኢንዲያን ኦሽንን የመሣሠሉ ድረገፆች እንደሚያደርጉት ለንባብ ክፍያ አይጠይቁም። ስለዚህ ይህንን ያህል መድረኩ ላይ የመቆየታችው ምክኒያት ጥያቄ ቢያስነሳ የሚገርም አይሆንም።

ጣቢያው ለምን ተዘጋ

መላምቶችን ማስቀመጥ አይከብድም። ኢኤንኤን የመንግሥትን ሙሉ ድጋፍ እንደሚያገኝ ተማምኖ የተከፈተ ድርጅት ይመስላል። ድጋፉ በቀጥታ የበጀት ድጎማ፥ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ማስታወቂያ፥ እንዲሁም የተለያዩ ስፖንሰርሺፖች ናቸው። መመዘኛቸው ምን እንደሆነ ባይታወቅም በሀገሪቱ ግዙፍ የሆኑት የህዝብ ንብረቶች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፥ ኢትዮ ቴሌኮምና የመድን ድርጅት ለቴሌቪዥን ጣቢያው እገዛ ያደርጉ ነበር። ድርጅቶቹ ለውጡን ተከትሎ እጃቸውን መሰብሰባቸው ድሮም ከትርፍ ይልቅ ከፖለቲካውን ጋር መንፈስ ዋነኛ ግባቸው እንደሆነ አመላካች ነው። ሌላው እዚህ ጋ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር “ባለፀጋው ሼህ ሞሐመድ አልዐሙዲ በሳውዲ ዓረቢያ እስር ላይ መሆናቸው የጣቢያውን ሞት አፋጥኖት ይሆን?” የሚለው ነው። የድርጅቱ ባለቤት ለባለፀጋው ቪዲዮ ይሰሩ እንደነበር ሪፖርተር ጋዜጣ በእንግሊዝኛ እትሙ ገልጿል። ኢትዮጵያ ፈርስት በተባለው ድረገፅም “የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ”፥ “የችግር ቀን ደራሹ”፥ “በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩት” የመሳሰሉ ማሞካሻዎች ይታያሉ። ምን ምን ባለበት እንደሚባለው ይሆን? ሼህ ሞሐመድ አልዐሙዲ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና አላቸው። በበጎ አድራጎት ተግባርም በሰፊው ይታወቃሉ። በፖለቲካው ውስጥ ወገንተኝነት ማሳየታቸውና ከባለሥልጣናት ጋር መሞዳሞዳቸው ግን አወዛጋቢ አድርጓቸዋል።

ኢኤንኤን በቴሌቪዥንነት መቀጠል የቻለው ለሁለት ዓመታት ነው። ወቅታዊ ሁኔታዎችን መዘገቡ፤ ጋዜጠኞቹን ልኮ ዜና መሰብሰቡ፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃተታ ማቅረቡ፤ እንግዶችን ጋብዞ ማወያየቱ፤ መዝናኛ ተኮር ከሆኑት ሀገር በቀል የግል የሣተላይት ስርጭቶች የሚለይበት በጎ ገፅታው ነው። የሰሞኑን አያድርገውና በተለያዩ ጋዜጣዊ መግለጫዎችና ሁነቶች ላይ የኢኤንኤን ዓርማ ያረፈበት ማይክረፎን ማየት ተለምዶ ነበር። በግልባጩ ደግሞ በሮች ሁሉ ክፍት እንደሆኑላቸውና የዜና ጥቆማ ከየአቅጣጫው ይደርሳቸው እንደነበር መረዳትም ይቻላል። እንደዛም ሆኖ በሀገሪቱ በቅርብ ዓመታት የተቀጣጠሉት እንቅስቃሴዎች የጣቢያውን ሩጫ አሳጥረውታል። ጣቢያው አጣብቂኝ ውስጥ ከገባባቸው ጉዳዮች መካከል ፤

  1. በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞን የተከሰተውን ግጭት ኢኤንኤን በሰበር ዜና መልክ ሲያቀርብ ተቃጠሉ የተባሉ ቤቶች ብሎ ያሳየው በአውስትራሊያ የሰደድ እሳት ምስል እንደሆነ ተደርሶበታል። ጣቢያው ስህተቱን አምኖ ይቅርታ ቢጠይቅም ታማኝነቱን ግን ክፉኛ ሸርሽሮታል።  
  2. ባለፈው ሰኔ 16 ቀን የጠ/ሚ/ር አብይ አህመድን አመራር በመደገፍ የተካሄደውን ሰልፍ ባለመዘገቡ ነቀፋ ተሰንዝሮበታል። ከ13 ዓመት በፊት ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲን በመደገፍ ከወጣው በኋላ በሀገሪቱ በዚህ ሁኔታ የታየ ሰልፍ አልነበረም። ይሁንና ኢኤንኤን ለጉዳዩ ትኩረት ነፍጓል በሚል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ማብራሪያ ጠይቋል። ኢብባ እንደዚህ አይነት ጥያቄ ለማቅረብ ሕጉ ይፈቅድለት እንደሁ ቢያከራክርም ድርጅቱ ግን “ዘጠኝ ያህል” ዜናዎችን እንደሰራ ለባለሥልጣኑ በሰጠው ምላሽ አሳውቋል::

የኢኤንኤን ከመድረኩ መውጣት ጥሩ ዜና አይደለም። ምንም አይነት አቋም ይኑረው አንድ ሃሳብን መግለጫ መሣሪያ ነው። ሁሉም መገናኛ ብዙሃን በአንድ ወንዝ እንዲፈሱም አይጠበቅም። የመጫወቻ ሜዳውን ግን ለሁሉም እኩል መስተካከል አለበት። ኮረኮንችም ሆነ ሳር።

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: